አለም አቀፍ የእባብ ንክሻ ግንዛቤ ቀን፡ በኢትዮጵያ የእባብ ንክሻንየተሻሻለ የህክምና መተግበሪያ እቅድ ስለማውጣት
Snakebite

አለም አቀፍ የእባብ ንክሻ ግንዛቤ ቀን፡ በኢትዮጵያ የእባብ ንክሻንየተሻሻለ የህክምና መተግበሪያ እቅድ ስለማውጣት

የእባብ ንክሻ በዓለም ላይ በጣም ችላ ከተባሉት የቆላማ በሽታዎች አንዱ ነው። የእባብ ንክሻ በዓመት ከ81,000 እስከ 138,000 የሚደርሱ ሰዎችን የሚገድል ሲሆን፣ በርካቶችን ህይወት ለሚለውጥ አካል ጉዳተኝነት ይዳርጋል። የእባብ ንክሻ እ.ኤ.አ. በ2019 አባል ሀገራት በተስማሙት ፍኖተ ካርታ ላይ በዓለም ጤና ድርጅት ከተካተቱት 20 ችላ ከተባሉት የቆላማ አካባቢ በሽታዎች አንዱ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2030 በእነዚህ በሽታዎች የሚደርሰውን ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ያለመ ፍኖተ ካርታ ነው።


የአለም ጤና ድርጅት ግቦችን ለማሳካት የመፍትሄው አካል የሆኑት ውጤታማ ፀረ-የእባብ መርዞችን እና የአለም አቀፍ ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍን ማረጋገጥን ጨምሮ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥረቱ የሚቀጥል ሲሆን በእባብ ንክሻ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከሰባቸው ሀገራት መንግስታት እና የአካባቢ ማህበረሰቦችም ትልቅ ሚና አላቸው። የእባቡ ንክሻ ህክምና ወደ ህክምና ተቋማት ይበልጥ በቀረበ መጠን ምላሹ ፈጣን እና የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በብቃት ምላሽ ለመስጠት በደንብ የታሰበበት፣ ሁሉንም የሚመለከታቸው ተዋናዮችን ያካተተ፣ እና ወሳኝ በሆነ መልኩ በቂ ሃብት ያለው እቅድ መውጣት አለበት።


ዶ/ር አለን ፔሬራ ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የኤም.ኤስ.ኤፍ የህክምና አስተባባሪ ሆነው አገልግለዋል። በዚያን ጊዜ፣ በፕሮግራሞቻችን ውስጥ የእባብ ንክሻ ያጋጠማቸውን ታካሚዎች በማከም የፕሮጀክት ቡድኖችን መደገፍን ጨምሮ በብዙ የህክምና ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል። የእባብ ንክሻን ለመከላከልም በአገር አቀፍ ደረጃ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እየሰሩ ነው። በዚህ ቃለ መጠይቅ ዶ/ር ፔሬራ ልምዳቸውን አካፍለውናል።
 

ጥያቄ፦ ጤና ይስጥልን! ዶ/ር ፔሬራ፣ ኤም.ኤስ.ኤፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የእባብ ንክሻን በመዋጋት ላይ ያለውን ተሳትፎ በመግለጽ መጀመር ይችላሉ?

መልስ፦ ኤም.ኤስ.ኤፍ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ 20 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በዋናነት እንደ ካላዛር ካሉ ሌሎች ችላ ከተባሉ የቆላማ አካባቢ ህክምና በመስጠት ላይ ይገኛል። በአካባቢው በየአመቱ ጥጥ ወይም ሰሊጥ ለመሰብሰብ ለስራ የሚመጡ በርካታ ሰራተኞች ከሌሎች አካባቢዎች ይመጣሉ። በማሳ ላይ እየሰሩ ወይም ከማሳው በቅርብ ርቀት በሌሊት ሲተኙ አብዛኛውን ጊዜ በእግራቸው ወይም በእጃቸው ላይ በእባቦች ይነደፋሉ።

... 2014 አካባቢ፣ ኤም.ኤስ.ኤፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን መደገፍ የሚችልበት የእባብ ንክሻ ህክምና ክፍተት እንዳለ ተገነዘብን። ስለዚህ የእባብ ንክሻን ማከም ጀመርን እንዲሁም ስራችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየጨመረ መጥቷል። ባለፉት ዓመታት ኤም.ኤስ.ኤፍ በገጠር የአብዱራፊ ማህበረሰብ ውስጥ ነፃ እና ጥራት ያለው የእባብ ንክሻ ህክምናን (የፀረ-የእባብ መርዝ መድሃኒት /አንቲቬኖሞችን ጨምሮ) እየሰጠ መሆኑን ገልጿል። በአካባቢው ይህን አገልግሎት የምንሰጥ እኛ ብቻ ነን። ዛሬ አብዱራፊ በአለም ዙሪያ ካሉ ፕሮጀክቶቻችን ውስጥ የእባብ ንክሻን የምናክምበት ትልቁ የኤም.ኤስ.ኤፍ ተቋም ነው። ... 2023 ብቻ በፕሮጀክቱ ውስጥ 1,753 ለእባብ ንክሻ ታካሚዎች ህክምና አድርገናል።

ጥያቄ፦ ሰዎች የእባብ ንክሻ ሕክምናን በሚያገኙበት ጊዜ የሚያጋጥሟቸው እንቅፋቶች አሉ?

መልስ፦ አንድ ሰው በእባብ ከተነደፈ በኋላ ወደ ጤና ማእከል ለመድረስ የሚወስደው ጊዜ በጣም ወሳኙ ጉዳይ ነው። ሆኖም፣ አብዛኛዎቹ የእባብ ንክሻ ኬዞች ከማንኛውም የጤና ተቋም በጣም ርቀው በገጠር ወይም ራቅ ባሉ አካባቢዎች ይከሰታሉ። እንዲሁም አብዛኞቹ ተጎጂዎች ብዙ ጊዜ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና እንክብካቤ መስጫ ቦታ የሚደርሱበት የትራንስፖርት አቅርቦት አለማግኘት በራሱ ለህክምና እንቅፋት ይሆናል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ያለው ግጭት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንቅስቃሴን ከመገደብ አንፃር ችግሩን እያባባሰ ነው።

ሁለተኛው እንቅፋት በጤና እንክብካቤ ተቋማት ውስጥ የፀረ-የእባብ መርዝ መድሃኒት አቅርቦት ውስንነት መኖሩ ነው። ሌላው ፀረ-የእባብ መርዝ መድሐኒቶች አስተማማኝ ቀዝቃዛ ማከማቻ ያስፈልጋቸዋል። እንዲሁም መድሃኒቶችን በትክክለኛው ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ማቆየት የሚቻልበት ቦታ ብዙ ጊዜ በሩቅ ቦታዎች አይገኝም። ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ለታካሚዎቹ እራሳቸው የሚገዙ መድኃኒቶች በጣም ውድ ናቸው። በኤም.ኤስ.ኤፍ ክሊኒኮች ውስጥ ያሉ ታካሚዎች ነፃ ህክምና ያገኛሉ።

ሌላው ችግር ከምርመራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፖሊቫለንት የፀረ-የእባብ መርዝ መድሃኒት የለም - ማለትም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የእባቦች ዓይነቶች ላይ ውጤታማ የሆነ ፀረ-እባብ መርዝ መድሃኒት የለም ማለት ነው። ክሊኒኮች የታካሚውን የሕመም ምልክቶች መመርመር አለባቸው፡፡ እነዚህ ልዩ ምልክቶች ታካሚወን ከነከሰው የእባቡ አይነት ጋር በማገናኘት በዚህ መሰረት ውጤታማ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን ፀረ-የእባብ መርዝ መድሃኒት መምረጥ ይጠበቅባቸዋል።

ለሰዎች በሚቀርበው ውስን የፀረ-የእባብ መርዝ መድሐኒት አቅርቦት ዙሪያ ብዙ ጊዜ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ህክምናው ራሱ ፈታኝ የጎንዮሽ ጉዳቶችም ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ ታካሚዎች በሰለጠኑ ሰራተኞች ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል። በእባብ የተነደፉ ሰዎችን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ጊዜ እና ሀብት በጣም በዙ እናደሆነ በጣም ነው።

ጥያቄ፦ ብዙ ሰዎች የህይወት አድን ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ የእባብ ንክሻ ችግር እንዴት ሊፈታ ይችላል?

መልስ፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ የእባብ ንክሻ ችግር መሆኑን የምናውቅባቸው ብዙ አገሮች እስካሁን ድረስ የእባብ ንክሻን እንደ ትኩረት የሚያስፈልገው በሽታ ባለማየታቸው በብሔራዊ የጤና እቅዳቸው ውስጥ እንደ ችላ የተባሉ የቆላማ አካባቢ በሽታ አላካተቱትም። በኢትዮጵያ ሁኔታም በአካባቢው ያሉ ጤና ጣቢያዎች እና የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች በቀላሉ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ስለ እባብ ንክሻ ምንም አይነት ብሄራዊ መመሪያ የለም። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስካሁን ፍኖተ ካርታ አላዘጋጀም። እንዲሁም ይህን እቅድ አንዴ ከተዘጋጀ በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገዋል። እነዚህ ደግሞ ነገሮችን ወደፊት ለማራመድ የሚያስፈልጉ ቁልፍ እርምጃዎች ናቸው።

ጥያቄ፦ የእባብ ንክሻ ከዚህ በፊት እንደ ብሔራዊ የጤና ክብካቤ ትኩረት የሚሰጠው ተብሎ ያልተመዘገበው ለምን ይመስለሃል?

መልስ፦ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የጤና አጠባበቅን ጨምሮ ትኩረት እና ግብአት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ተግዳሮቶች ገጥሟታል።  የእባብ ንክሻ አንዱ ነው። ችግሩ በኢትዮጵያ እና እንዲያውም በአለም ላይ ምን ያህል ትልቅ ችግር እንደሆነ በእርግጠኝነት እየተገነዘብነው ይመስለኛል። ለምሳሌ፣ የሚኒስቴሩ የመረጃ ሥርዓቶች ስለ 'እንስሳ' ንክሻ መረጃን እንደ አንድ ምድብ ብቻ መዝግበው የሚይዙ ሲሆን፣ ያንን መረጃ በራሱ ምድብ ውስጥ የእባብ ንክሻ ብለው ለማሳየት አልከፋፈሉትም። ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህሉ በእባብ ንክሻ ተጎጂዎች በአገር አቀፍም ሆነ በሁሉም የጤና ተቋማት እንዳሉ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። የእባብ ንክሻን በጤና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዝርዝር ውስጥ ለመክተት የመጀመሪያው እርምጃ መረጃን በመሰብሰብ የችግሩን ስፋት ተጨባጭ እይታ መፍጠር ነው። ይህም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን አስፈላጊ ለሆኑት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቦታዎች ተስማሚ ሀብቶችን ለመመደብ ይረዳዋል።

በሰዎች ህይወት ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ ለማጉላት ችግሩን በአሃዝ መለካትና መግለጽም በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ተጠቂዎች እያንዳንዳቸው ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ያላቸው የሰው ልጆች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ብዙውን ጊዜ በጣም የሚጎዱት በእርሻ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች እንዲሁም ልጆች ናቸው።

ጥያቄ፦ የእባብ ንክሻ የድርጊት መርሃ ግብር ወይም ፍኖተ ካርታ ጠቅሰዋል፣ ይህን በተመለከተ ዋናዎቹ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

መልስ፦ የእቅዱ ዋናው እና የመጀመሪያ ነጥብ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ያልተማከለ እንዲሆን ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ ሰዎች ወደሚኖሩበት ቦታ በቅርበት ነፃና ጥራት ያለው ፀረ-የእባብ መርዝ መድሐኒት የሚያገኙባቸው ብዙ ተጨማሪ ማዕከላት ያስፈልጋታል። የእቅዱ ሁለተኛ ክፍል የህክምና ትቋማት በእባብ የተነደፉ ሰዎችን ለማከም በሚፈልጉበት ጊዜ በቀላሉ ሊከተሉት የሚችሉትን ብሄራዊ የእባብ ንክሻ መመሪያ ወይም ፕሮቶኮል መፍጠር ነው። ሦስተኛው ነጥብ ለፀረ-የእባብ መርዝ መድኃኒቶች የገንዘብ ድጋፍን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ይህም በተፈለገበት ቦታ እንዲገኙ ይደረጋል። አራተኛው ነጥብ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳቶች ባሏቸው እና በቀዝቃዛ ቦታ ማስቀመጥ የማያስፈልጋቸውን ባለብዙ ጠቀሜታ (ፖሊቫለንት) በሆኑ አዳዲስ ፀረ-የእባብ መርዝ መድሐኒቶች ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ማመንጨት ነው። ኤም.ኤስ.ኤፍ በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ ምርምር በማካሄድ ላይ ነው። ኤም.ኤስ.ኤፍ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የእባብ ንክሻ ለመከላከል የሚያስችል ይህንን ሰፊ እቅድ ለማዘጋጀት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገ ነው።

ጥያቄ፦ ወደ ሌላ የኤምኤስኤፍ ፕሮጀክት እየተሸጋገሩ እና ከኢትዮጵያ እየወጡ ነው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የእባብ ንክሻን ለመከላከል ለሚደረገው ስራ ያልዎ ተስፋ ምንድን ነው?

መልስ፦ በኢትዮጵያ ውስጥ የእባብ ንክሻ አስመልክቶ ሦስት ተስፋዎች አሉኝ።  የመጀመሪያው የእባብ ንክሻ በቅርቡ ችላ የተባለ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ዝርዝር ወስጥ ይካተታል። ዕውቅና ካገኘ በኋላ፣ ሁለተኛው ተስፋዬ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራ እና ሁሉም የጤና ባለሙያዎች የእባብ ህክምና ለመስጠት የሚያስችላቸው የድርጊት መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ ነው። ሶስተኛው ተስፋዬ ይህንን እቅድ ለመተግበር እና በተለይም የተሻሉ ፀረ-የእባብ መርዝ መድሐኒቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ ይገኛል የሚል ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላውን ችላ የተባለ በሽታ፣ በተባይ ንክሻ የሚከሰተው visceral leishmaniasis ወይም በተለምዶ ካላዛር (kala azar) የሚባለው ሲሆን፣ አሁን 20 ዓመታት በፊት ከነበርንበት የተሻለ የህክምና ደረጃ ላይ ደርሰናል። ያኔ፣ ያሉት ህክምናዎች መርዛማ የነበሩ እና ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ያልሆኑ ነበሩ። ዛሬ ላይ ካላዛርን ለመዋጋት ንቁ የሆነ ማህበረሰብ ከመኖሩም ባሻገር በኢትዮጵያም የሚፈልገውን የገንዘብ ድጋፍና ትኩረት አግኝቷል። ስለዚህ ይህን የስኬት ታሪክ በእባብ ንክሻ በኢትዮጵያ ለተጎዱ ሰዎች ለመድገም ተስፋ እናደርጋለን።

ጥያቄ፦ ከኢትዮጵያ ምን ትምህርት መውሰድ ይቻላል?

መልስ፦ በህንድ፣ ባንግላዲሽ እና ሌሎች ቦታዎች ለኤም.ኤስ.ኤፍ እንደመስራቴ በእባቦ ለተነደፉ ሰዎች ውጤታማ የሆነ የአንቲቬኖም ህክምና ለማግኘት ተመሳሳይ ፈተናዎችን አይቻለሁ። የብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ቁልፍ ነው፡፡ ነገር ግን እቅዱን ለመተግበር የገንዘብ ድጋፍ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
በብዙ ሁኔታዎች፣ መንግሥት ብቻውን የፋይናንስ ሸክሙን ሊሸከም አይችልም፣ ታካሚዎችም በቀላሉ መድሃኒቱን ለመግዛት ገንዘብ የላቸውም። በተጨማሪም፣ ለአዳዲስ ምርመራዎች እና ህክምናዎች ተጨማሪ ምርምር አስፈላጊ ነው። በአለም ዙሪያ ያለውን የእባብ ንክሻ ህክምና ችግር ለመቅረፍ አለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ መስጠት አለባቸው።
 

Up Next
Malaria
Article 28 November 2024